ስልተ ፍሰት/urinary system

ስልተ ፍሰት (urinary system ) ኩላሊትን፣ ቅድመ ቀጂን፣ ፊኛንና ድህረ ቀጂን ይጨምራል።

በዶ/ር ፍቃዱ አየለ/By Dr Fekadu Ayele

11/10/20251 min read

እልፍ ምንጮች - የኩላሊት አወቃቀርና ተግባር

ውድ አንባቢዎች፣ ይህንን የጤና መረጃ ስለኩላሊት አወቃቀርና ተግባር ለእናንተ አቅርቤያለሁ።

የኩላሊት አጠቃላይ መዋቅር

ሁላችንም ሁለት ኩላሊቶች አሉን - የግራና የቀኝ። እነዚህ የአደንጓሬ ቅርጽ ያላቸው አካላት በመሃል ጎናቸው ላይ ስርጉደት አላቸው። ይህ ስርጉደት (hilum) ደም ስሮችና ሌሎች አካላት የሚገቡበትና የሚወጡበት በር ነው። ኩላሊቶች በባህረ ሆድ ውስጥ በጀርባ በ ጎን እና ጎን በኩል ይገኛሉ። የቀኝ ኩላሊት ጉበት ስለሚጫናት ከግራ ይልቅ ትላለች።

ኩላሊቶች በሶስት ሽፋኖች ተጠቅልለዋል። የውጪው የኩላሊት ታካኪ ስብ (pararenal fat)፣ መሃል ላይ የኩላሊት ልባጥ (renal fascia) እና ወደውስጥ የኩላሊት ዙሪያ ስብ (perirenal fat) ናቸው። እጅግ ወደውስጥ የምንገባ ከሆነ የኩላሊት ከፈን (renal capsule) የሚባል ቀጥተኛ ሽፋን አለ።

የኩላሊት ውስጣዊ አወቃቀር

ኩላሊትን መሃል ለመሃል ስንሰነጥቃት ሶስት ዋና ደርቦችን እናያለን፡

1. የኩላሊት ቅርፊት (Cortex) - የውጪው ክፍል ሲሆን ወደውስጥ የሚዘረጉ ምሰሶዎች (renal columns) አሉት።

2. የኩላሊት እምቡጠት (Medulla)- የኩላሊት ፒራሚዶች ስብስብ ነው። እነዚህ ፒራሚዶች ጫፋቸው ከኩላሊት ጡትማ (renal papilla) የተዋቀረ ነው። አንዲት የኩላሊት ድብልልት (renal lobe) አንድ ፒራሚድና በዙሪያው ያለውን ቅርፊት ትጨምራለች።

3. መሃል ቀጂና አላቢዎች - መሃል ቀጂ (pelvis) የተዋቀረው ከንኡስ አላቢዎች (minor calyces) እና ከአበይት አላቢዎች (major calyces) ተዋረድ ነው። እነዚህ ሽንትን ወደ ሽንት ቱቦ የሚያስተላልፉ የውሰጠኛ ክፍል ናቸው።

የኩላሊት ደምስሮች ስርዓት

የኩላሊት ደም ዝውውር እጅግ ረቂቅና ውስብስብ ነው። ዝውውሩ የሚጀምረው ከሆድ አውራቀጂ ላይ በሚነሳው የኩላሊት ደምቅዳ ነው። ይህ ደምቅዳ ተከታታይ ቅርንጫፎችን ይሰጣል፡

የኩላሊት ደምቅዳ (renal artery) → ተግመስማሽ ደምቅዳ (segmental artery) → ድብልልት አቋራጭ ደም ቅዳ (interlobar artery) → ደጋንማ ደምቅዳ (arcuate artery) → ቅርፊታዊ ተፈንጣቂ ደምቅዳ (cortical radiating artery)።

ከተፈንጣቂ ደምቅዳዎች አብሳሪ ደምስሮች (afferent arteries) ይነሳሉ። እነዚህ የሚፈጥሯቸው አጠንፋፊዎች (glomeruli) ደምን የሚያጣሩትl ልዩ የደምመርብ አይነቶች ናቸው። ከአጠንፋፊዎች ደም በ አከናዋኝ ደምስሮች (efferent arteries) ወጥቶ የአሸንዳ ዙሪያ የደምስር ሐረጎችን (peritubular capillaries) ይፈጥራል።

ከአብሳሪ ደምስሮች በተጨማሪ አቆልቋይ ደምስሮች (vasa recta) ተብለው የሚጠሩ ቁልቁል ወደ እምቡጠት የሚወርዱ ቅርንጫፍ አላቸው። እነዚህ ሽንትን የማወፈርና የማቅጠን ተግባር ያከናውናሉ።

ደሙ መጨረሻ በደጋንማ እና በድብልልት አቋራጭ ደምመልሶች አድርጎ ወደ የኩላሊት ደምመልስ ገብቶ ወደ ታቻዊ ደምመልስ ይገባል።

የኩላሊቶች ውስብስብ አወቃቀር ለሰውነታችን ደም ማጣሪያና ሚዛን ማስጠበቂያ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በሚቀጥለው ክፍል የሽንት መፍጠሪያ ዘዴዎችን በዝርዝር እንመለከታለን።

ምንጭ፡ ዶ/ር ፍቃዱ አየለ - ማህደረ ጤና ኢትዮጵያ
በዝርዝር ለመረዳት የዩቲውብ ቻነላችንን ይጎብኙ